ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተመራቂዎቹን ቁጥር 39684 አደረሠ፡፡

  • -

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተመራቂዎቹን ቁጥር 39684 አደረሠ፡፡

Print Friendly, PDF & Email

 

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የ2011 ዓ.ም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ሲያሰለጥናቸው የነበሩትን ሰኔ 29 በዋናው ግቢና ሰኔ 30 በቡሬ ካምፓስ በደማቅ ዝግጅት አስመረቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለ11ኛ ዓመት ባካሄደው የተማሪዎች የምረቃ በዓል ላይ 5028 ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ከእነዚህም ውስጥ 35 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ በቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ በመደበኛውና በርቀት ትምህርት ፕሮግራም ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩት የዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች በየደረጃው በተደረገው ግምገማና በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ውጤታቸው ታይቶ ነው የተመረቁት፡፡

በምረቃ በዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሥራ አመራር አባላት ሰብሳቢ ዶ/ር ፍፁም አሰፋ ናቸው፡፡ ለተመራቂዎች መልዕክት ያስተላለፉት ዶ/ር ፍፁም አሠፋ አገራችን ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ የተማረ የሰው ሃይል የምትፈልገበት የለውጥ ጊዜ ላይ በመመረቃችሁ ደስ ሊላችሁ ይገባል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ፍፁም አያይዘውም መማር መመራመር ለአገር እንዲበጅ ተብሎ የሚደረግ ስለሆነ ለምረቃ እና ለድል መብቃታችሁ ሊያስመሰግናችሁ ይገባል፤ የምትመርቃችሁም አገር ናት ብለዋል፡፡

በዓመቱ ውስጥ በርካታ ችግር አልፋችሁ ለዚህ መብቃታችሁ የጠባሳችሁን ሳይሆን የፈውሳችሁን መንገድ ለመቀየስ ባላችሁ ቁርጠኝነት ስለሆነ የዛሬው ምርቃታችሁ ከምንጊዜውም በላይ ለእናንተ ክብርና ሞገስ ያጎናፅፋችኋል በማለት ዶ/ር ፍፁም የተማሪዎችን የአንድ ዓመት ሠላማዊ ቆይታ አድንቀዋል፡፡ ዶ/ር ፍፁም በመጨረሻም አገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት የለውጥ ጊዜ እንደመሆኑ ተመራቂዎች ለለውጡ ድጋፍና አጋዥ እንዲሆኑም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ በበኩላቸው በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ ወጣትነት በታመመ ፖለቲካ ውስጥ ፖለቲካው ሳይረዱ ለሃገር ተጨማሪ ህመም ከመሆን ይልቅ የተሻለ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ህዝብ በማገልገል የትምህርት ውጤቱን ማሳየት አስፈላጊ እንደሆነ በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ታፈረ አያይዘውም ተመራቂዎች ከምንም በላይ የወጣትነት ጊዜያቸውን በቀደምት አባቶቻቸው አስተምሮና ጠንካራ እሴት ላይ በማነፅ ለሃገር አለኝታ የሚሆንበት መንገድ ስለሆነ የአባቶችን አርቆ አሳቢነትና ነባይነት መላበስ እንደሚገባ ለተመራቂዎች አስገንዝበዋል፡፡

ዶ/ር ታፈረ መላኩ በርካታ ወጭ አውጥታ ያስተማረችን አገር ውለታ ለመክፈል ከምንግዜውም በላይ ድርብ ሃላፊነት የሚወጡበት ጊዜ ስለሆነ ምክንያታዊነትና የሃሳብ ብዝሃነትን የሚያስተናግዱ መሆን እንዳለባቸው መክረዋል፡፡ ዶ/ር ታፈረ ሲያጠቃልሉም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሁሉም አልጋ በአልጋ ባይሆንላቸውም ባለው የሃገርና የህዝብ ውስን ሃብት እናንተን ለዚህ ለማብቃት ብዙ ለደከሙ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞች ምስጋና አቅርበው ለተመራቂዎች መልካም ምኞት ለቤተሰቦቻቸው ደግሞ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በ11ኛው ዙር የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ በዓል ላይ ከተመረቁት መካከል 763 የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት ከሚሰጠው 1 የሶስተኛ ዲግሪ፣ 48 የሁለተኛ ዲግሪና 54 የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች በተጨማሪ በቀጣይ ዓመት በገበያ ፍላጎት የላይ የተመሰረቱ ፕሮግራሞችን ከፍቶ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት የሥርዓተ-ትምህርት ቀረፃና ክለሳ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ አብላጫ ውጤት ላመጡ ተመራቂዎች የሰርተፊኬት፣ የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት እንዲሁም የመዝናኛ ፕሮግራም የዝግጅቱ አካል ነበር፡፡

 


Search DMU

Upcoming Events

There are no upcoming events.

Partners

DMU Radio Broadcasting . . .